የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በአንባሰል ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ተገኝቶ " አምባሰል ለገደል ፥ ምን? ያሽሟጥጡታል ፈረስ ባያስጋልብ ፥ " ማር! " ይቆርጡበታል! " ይለናል። ሲወርድ ሲዋረድ ከአባቶቹ ያገኘው ሥነ ቃል ነው። በነገራችን ላይ " ማር! " የሚለው ዝም ብሎ እንደ እንግዳ ደራሽ ፥ እንደ ውኃ ፈሳሽ ዝም ብሎ ለሥነ ቃል ማሳመርያ የገባ አይደለም። ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው። አምባሰል በአማራ ክልል ኢትዮጵያ የሚገኝ ወረዳ ሲሆን በወረዳው ውስጥ የሚገኘው አምባ ወይም የግሸን ተራራ መታወቂያው ነው። አምባሰል የሚለው ቃል አምባ እና አሴል ከሚለው ሁለት ቃል የተገኘ ሲሆን አምባ ማለት ተራራ “አሴል” ማለት ደግሞ የአረበኛ ቃል ነው ትርጉሙም ማር ማለት ነው። " የማር ተራራ ! " ፥ “የማር መሬት” እንደ ማለት ነው። በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኘው አምባሰል ወረዳ በምዕራብ፦ በሺሎ ወንዝ ተንታ ፣ በሰሜን፦ ሰሜን ወሎ ዞን፣ በደቡብ ምስራቅ፦ ሚሌ ወንዝ ተሁለደሬ፣ በደቡብ፦ ኩታበር ያዋስነዋል። ከተማው ደግሞ ውጫሌ ይሰኛል። ከቀዳማዊው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ቀዳማዊው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ድረስ የአምባሰል አውራጃ ገዥ የቤተ አማራ (ወሎ) ግዛት አስተዳደር ጃንጥራር ይሰኝ ነበር። እቴጌ መነን አስፋው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ባለቤት የአምባሰል ጃንጥራር አስፋው ልጅ ነበረች።