ዛሬ መስከረም 21 ፥ ዕለተ ቅዳሜ ፥ 2015 ዓ.ም አንባሰል ፥ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በሚሉዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ደምቆ እየተከበረ ይገኛል።
ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በአሁኑ ወሎ ክፍለ ሃገር፣ አምባሰል ወረዳ ፥ በግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ ቤ/ክርስቲያን ናት።
የቤ/ክርስቲያኗ መግቢያ መንገድ አንድ ብቻ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ቤተ ክርስቲያኗ በየዘመኑቱ የተለያየ ስያሜ አሏት።
ከአጼ ድልናአድ ዘመን 866 ዓ.ም እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ " ደብረ ከርቤ " በመባል ትታወቅ ነበር።
በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤ/ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዜአብሔር በሚል ስም ተጠራች።
ብዙ ሳይቆይ ደግሞ ደብረ ነገስት ተባለች።
በ1446 አጼ ዘርአ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን በዚህ ስፍራ ሲያመጡ ደብረ ነገስት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች።
በዚህ ጊዜ የነበረው የቤ/ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ " መምህረ እስራኤል ዘ ደብረ ከርቤ! " ይባል ነበር።
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ "ገሰ" ወይም በአማርኛው "ገሰገሰ" የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ። አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ።


Comments
Post a Comment