Skip to main content

እጅ የበዛበት የኦሮሞ ፖለቲካን መምህር ወንድ ወሰን ውቤ ነጽሮታል።


 የመጽሐፉ ርእስ፦ እጅ የበዛበት የኦሮሞ ፖለቲካ እና ኢትዮጵያዊነት

ጸሓፊ :- ዮሴፍ ከተማ ሆርዶፋ

የኅትመት ዘመን፦ ፳፻፲፫ ዓ.ም.

የገጽ ብዛት:- ፪፻፺፫

የሽፋን ዋጋ፦ ፻፴፭ ብር

     እጅግ ሰውኛ በኾነ የልጅነት አሳዛኝ ገጠመኙ መጽሐፉን ይጀምርልናል::   በአደገባት ግንደ በረት ወረዳ፣ ካቺሲ ከተማ ውስጥ የእርሱ ዘመን አፍቃሬ ኦነግ ወጣቶች ያደረጉት ፀረ-መንግሥት ዐመፅ ኪሮስ የተባለ መምህርን ቤተሰብ በማጥቃት ሲደመደም በልጅነት ሥነ ልቦናው ላይ የፈጠረበትን ጫና ያሳየናል።  ዐመፁ የብሔር ተኮር ጥቃት ገጽታ ሲይዝ አራስ የነበረችውን የመምህሩን ሚስት የኦሮሞ እናቶች ከልጆቻቸው ቁጣ መታደጋቸውን በእማኝነት ይተርክልናል።  

     ጸሐፊው ዲ. ዮሴፍ ከተማ በ0መፁ ወደ ዓመድነት ከተቀየረው ከመምህር ኪሮስ ቤት ፍርስራሽ ውስጥ አንዲት ደብተር ፈልጎ ያገኛል። የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ሚስቱ ኾና ትሞሽር የነበረችው የመምህር ኪሮስ ልጅ የሳባ ደብተር ነበረች። ከዛ በኋላ የልጅነት ነፍሱ በጥያቄ ስትዋከብ እናገኛታለን። 

ክስተቱን ሲገመግም፣ ጉድለቱን ነቅሶ ሲያወጣ፣ በአጠቃላይ እርሱ "የኦሮሞነቴ ፖለቲካ" እያለ የሚጠራውን የዘውግ ፖለቲካን በነጻ አእምሮ ሲታዘበው፣ ሲፈትሸው ሳየው የነፍሱ ቁንጅና ታየኝ። 

    በመጽሐፉ የኦሮሞ ፖለቲካ በስሑት ፍኖት ላይ እንዲገኝ ኢትዮዽያን ማፍረስ የሚፈልጉ አካላትን አጀንዳ በተሸከሙ ልኂቃን፣ በውጭ ጸሐፍት የተዛባ ታሪካዊ ዘገባ፣ የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት በሚቀነቀንበት የሶሻሊዝም እጅ እየታመሰ መኾኑን ያሳየናል:: በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በመሥራት ወሳኝ ሚና ካላቸው ሕዝቦች አንዱ የኾነው የኦሮሞ ሕዝብ እውነተኛ ሐሳቦችን የሚያደምጥ የፖለቲካ ምሕዳር መጥፋቱን በመረጃ ያመላክታል።

   ጸሐፊው በኦሮሚፋ "ሳብ-ቦና" (ኩሩ ብሔር) የሚል ጽንሰ ሐሳብ መኖሩንና ጽንሰ ሐሳቡም በቅኝ ግዛት ቀንበር ካለመገዛት ሥነ ልቡና የመጣ እንደኾነ ይነግረናል(ገጽ 13-14)። ይህ ነጻ ሕዝብ በ21ኛው ክ/ዘመንም ነጻ አውጭ አያስፈልገውም፤ ካስፈለገውም በግዝፈቱ ልክ እንደይገለጽ ከቀፈደዱት የጽንፈኝነት ፖለቲካ ነጋዴዎች ነው ነጻ መውጣት ያለበት በማለት ጠንካራ አቋሙን ያስቀምጣል። 

   በዚህ የሥነ ልቦና ውቅር ላይ የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ፖለቲካ በተንኮል የሮሮ ፖለቲካ ውስጥ እንዲዘፈቅ መደረጉን በቁጭት ያነሣል። ይህንንም የኦሮሞ ሕዝብ ባለፈበት የታሪክ ሒደት በተመሳሳይ ኹኔታ ያለፈን ሌላ ሕዝብ ታሪክ እያነፃፀረ ያቀርብልናል:: የመገንጠል ሓሳብ ይዘው ታገልን ያሉት ልኂቃኑ ትውልዱ ራሱን አናሳ አድርጎ እንዲመለከት ወደ ስሑት መንገድ ገፍተውታል። ይህን የጸሐፊውን ሓሳብ ደግሞ የስሑት መንገዱ ቀያሾች ከነበሩት አንዱ ሌንጮ ለታ ለጋዜጠኛና ጸሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ በጸጸት መልክ ነግረውት፣ ከዚህ መጽሐፍ ጋር በተመሳሳይ ወርና ዓመት በታተመውና ፍልስምና ፮ በተሰኘ መጽሐፉ አስቀምጦልናል።  


የዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማም:-

👉 ለሀገራዊ አንድነት የሚበጁ ነገር ግን ያልተደመጡ የኦሮሞ ሕዝብ ሐሳቦች እንዲደመጡ ማድረግ። ይኽም ፖለቲካው በትክክለኛ፣  አዎንታዊ በኾነውና የኦሮሞ ሕዝብ ይበልጥ በሚጠቀምበት መንገድ እንዲጓዝ ማድረግ መኾኑን ደጋግሞ ይነግረናል። (ገጽ 12 ፣ 17፣ 154 ፣ 185) ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነት የነገሡ ሐሰቶችንና የተድበሰበሱ እውነቶችን ፍለጋ ባደረገው ቅኝትም በርካታ ነገሮች ነቅሶ ያወጣል። 


   ኦነግ ከኦሮሞ ሕዝብ ሥሪት በተቃረነ መልኩ በአማራ ሕዝብ እና ከየትኛውም ብሔር ኦርቶዶክስ ኾኖ በተገኘ ሁሉ ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ፍጅት ያጋልጣል፤ ያወግዛል:: 


    በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ የእርጎ ዝንብ የኾኑ እጆችን መንጥሮ ያሳየናል። ፖለቲካኞች እና የፕሮቴስታንት ቸርች ኦርቶዶክሳዊውን ኦሮሞ ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ለመነጠል በቅንጅት የተጫወቱትንና እየተጫወቱት ያለውን ፖለቲኮ ሃይማኖታዊ  ቁማር ያስቃኘናል። ለአብነትም የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እንመሠርታለን ብለው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጀርባ ያለውን ሴራ ገላልጦ አስቀምጦልናል። 

   የአንዲት ሀገር ልጆች እንደመኾናችን ለአብሮነታችን አንዱ ችግር እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ራሱን እንዲህ ነኝ ባለው መጠን ዕውቅና ያለመሰጣጣት መኾኑን ያሠምርበታል(ገጽ 13 ፣ 149)::

ጸሐፊው ተግዳሮቶችን፣ ሴራዎችን በመግለጡ ዓላማውን እንዳሳካ ቆጥሮ "ሩጫዬን ጨርሻለሁ" አይልም። ፈተናዎቹን መሻገሪያ፣ ሴራዎቹን ማክሸፊያ መፍትሔዎችን ይጠቁመናል። 

የታዩኝ ክፍትቶች :-

👉የዋቢ አጠቃቀስ ቢሻሻል። ለምሳሌ አንዳንድ የሚታወቁ ሐሳቦች ምንጫቸው ሳይጠቀስ ታልፏል፤ አንዳንድ ምንጮች በግርጌ ማስታወሻ ይጠቀሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ በዋቢ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ እንኳ አይገኙም፡፡ ሌላው ደግሞ የአንድን ጸሐፊ ጽሑፍ ሙሉ ለሙሉ ከማካተት ጭምቁን ማካፈል የተሻለ ነው እላለሁ።

👉 የሆሄ አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ተደርጓል። ነገር ግን አሁንም በጥቂቱ ይቀረዋል፡፡ በሚቀጥለው ኅትመት የቃላት ግድፈት በደንብ ቢታይ ጥሩ ነው::

      በመጨረሻ በጸሐፊው አንድ ምክር ዳሰሳውን ልቋጭ ፦" ፖለቲካኞቻችን ለችግራችን ተጠያቂ ማፈላለግ ትታችሁ መፍትሔ ፈልጉልን።"

ዲ. ዮሴፍ ከተማ ሆርዶፋ ሚዛን ለጠበቀ ሥራህ እናመሰግናለን🙏

Comments

Popular posts from this blog

አርሲ እና የአርሲ ሴቶች ባህል

  በዳዊት ፀሐይ አርሲ በማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክፍል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኝ ክልል ነው።  በዋናነት በአካባቢው በሚኖሩ በአርሲ ሰዎች ስም ተሰይሟል።  የአርሲ ዞን ወደ 17,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖራል።  ክልሉ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች የሚታወቅ ሲሆን ይህም ደጋ፣ ቆላማ እና ደኖችን ያጠቃልላል።  በተጨማሪም የላንጋኖ ሀይቅ እና የዝዋይ ሀይቅን ጨምሮ የበርካታ ወንዞች እና ሀይቆች መኖሪያ ነው።  በአርሲ ያሉ አብዛኛው ሕዝብ ዋናው የገቢ ምንጭ ግብርና ነው።  ክልሉ ቡና፣ ሻይ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና ሌሎች ሰብሎችን በማምረት ይታወቃል።  የእንስሳት እርባታ የኢኮኖሚው አስፈላጊው አካል ነው። አርሲ ካሏት ባህላዊ ቅርሶቿ በተጨማሪ የበርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ባለቤትም ናት።  ከእነዚህም መካከል በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጀመረው አዳዲ ማርያም ውቅር ቤተ ክርስቲያን እና የሶፍ ኦማር ዋሻ ( ከአፍሪካ ትልቁ የዋሻ ስርዓት አንዱ ነው። ) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፠ በአጠቃላይ አርሲ ልዩ የሆነ ባህልና ታሪክ ያላት በመልክአ ምድርና በተፈጥሮ ሀብት በእጅጉ የበለጸገች  ክልል ናት። በአርሲ ባህል ሴቶች ትልቅ ሚና አላቸው።  ቤተሰብን የማስተዳደር፣ ልጆችን የማሳደግ እና በቤተሰቡ ገቢ ላይ በእርሻ ወይም በትንንሽ ንግዶች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው።  ሴቶች በማህበረሰብ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች በተለይም ከማህበራዊ ደህንነት እና ልማት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። በአለባበስ ረገድ የአርሲ ሴቶች በተለምዶ ሸማ የሚባል የባህል ልብስ ይለብሳሉ። ከጥጥ የተሰራ እና በቀለማት ያሸበረቀ ነው።...

ነጻ የወጣችውን ራያ ቆቦን ወገን ለመቼ ነው በሚል ስፍራው ጋ ደርሰን የህዝቡን አኗኗር እና ስነ ልቦና አይተናል።

   ከብዙ በጥቂቱ ፥ ከሙሉ በክፍሉ ነጻ የወጣችውን ራያ ቆቦን ወገን ለመቼ ነው በሚል ስፍራው ጋ ደርሰን የህዝቡን አኗኗር እና ስነ ልቦና አይተናል።ከሁለት ዓመት በውኋላ ተቋርጦ የነበረው መብራት ስለ መጣ ከተማው በተኩስ ሲናጥ አድሯል።   ቆቦ በሰሜን ኢትዮጵያ ÷ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኝ ከተማ ናት  ቆቦ ከባህር ጠለል በላይ 1468 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች።   ቆቦ በምዕራብ በኩል በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች እና በምስራቅ በአፋር የእሳተ ጎሞራ ጭንቀት ያዋስናታል።  በታሪክ ራያ አንጎት ተብላ ትጠራ ነበር። ራያ ቆቦ የአማራ ህዝብ ነው። አንጎት በአማራ ክልል ወልድያ አቅራቢያ ከሀብሩ ወረዳ በደቡብ በኩል እስከ ማይጨው ራያ አዘቦ የሚደርስ ሜዳ ነው።  ይህ ስፍራ ከኢፋት ሱልጣኔት (13ኛው ክፍለ ዘመን) ጊዜ ጀምሮ በክርስቲያን ደጋማውያን እና በምስራቅ በመጡ ሙስሊሞች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ውስጥ ነበር።  አብዛኛው ቀደምት ግጭት የተካሄደው በደቡብ በኩል በምስራቅ ድንበር ነበር። አሁን ሸዋ ነው።   ነገር ግን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንጎት አሁን ራያ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአዳል ጀነራል አህመድ ኢብኑ ኢብራሂም አል-ጋዚ ጦር እና በኢትዮጵያው አጼ ልብነ ድንግል ከፍተኛ ግጭት ጊዜ የውጊያ መዐከል ነበር። ይህ አስነዋሪ የግጭት ዘመን የኢትዮጵያና የአዳል ጦርነት በመባል ይታወቅ ነበር።  አጼ ልብነ ድንግል የካቲት 10 ቀን 1541 ምጽዋ ወደብ ከደረሱት ፖርቹጋሎች እርዳታ ጠየቁ። በሚያዚያ ወር 1542 የሁለቱ ሠራዊት ከአሸንጌ  ሃይቅ በስተሰሜን በኮረም አካባቢ ተገናኙ። ይህም ውጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ጦር መ...

የወላይታ ንጉስ ካኦ ጦና

በዳዊት ፀሐይ  ካኦ ጦና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የገዛ የወላይታ ንጉስ ነበር።  ወላይታ በደቡብ ኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሚገኝ ክልል ነው።  የራሱ የሆነ ቋንቋ እና ባህል ያለው የወላይታ ህዝብ መኖሪያ ነው።  ክልሉ በቡና ምርት የሚታወቅ ሲሆን በተፈጥሮ ውበቱ የቱሪስት መዳረሻም ነው።  እናም ካኦ ጦና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን የኢትዮጵያን ግዛት መስፋፋት በመቃወም ይታወቃሉ።  ካኦ ቶና ህዝቡን እየመራ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ተከታታይ ጦርነት ቢያደርግም በመጨረሻ ግን ተሸንፎ እጅ ለመስጠት ተገደደ።  በስደት ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ኖረ።  ካኦ ቶና ቢሸነፍም በወላይታ ህዝብ ዘንድ እንደ ጀግና ሲታወስ ቆይቷል።  ትሩፋቱ በወላይታ አፈ ታሪክ እና ዘፈኖች የተከበረ ሲሆን ታሪኩ አሁንም ጭቆናን እና ኢፍትሃዊነትን ለመቃወም ይውላል። ስለ ጦርነቱ ማለትም ስለ ካኦ ጦና እና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መካከል ስለተደረጉ ጦርነቶች ዝርዝር መረጃ ማግኘት ይቻላል።  ሆኖም ካኦ ጦና ህዝባቸውን በመምራት በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ተከታታይ የሽምቅ አይነት ጥቃቶችን ማለትም እንደ ማሸማቀቅ እና መምታት የመሳሰሉ ስልቶችን ሲጠቀሙ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አመፁን ለመደምሰስ ብዙ ጦር ልከው ነበር።  ጦርነቱ ለብዙ አመታት የዘለቀ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል።  በመጨረሻም ካኦ ጦና ተሸንፎ እጅ ለመስጠት ተገዷል።  በስደት ወደ አዲስ አበባ ተወስዶም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ኖሯል። ፊታውራሪ ደስታ ፍስሐ የካኦ ጦና ልጅ